Tuesday, February 5, 2019

በየደረጃው የሚገኙ ባለሙያዎችና የአመራር አካላት መብትና ግዴታቸውን አውቀው የየተቋማቱን ዕቅድ ለማሳካት እንዲችሉ በሰራተኞች የመተዳደርያ ደንብ ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ይበልጥ ማሳደግ እንደሚገባ ተጠቆመ ፡፡ ለአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ፅ/ቤት እና በስሩ ለሚገኙ 18 ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች የሰው ሃብት ሰራተኞች እና አመራሮች ስልጠና ተሰጥቷል ፡፡ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት የሰው ሃብት አስተዳደር ደጋፊ የስራ ሂደት መሪ አቶ ጃምቦ ብርሃኑ ለሁለት ቀናት በተሰጠው ስልጠና ላይ ባደረጉት ንግግር በየወቅቱ የሚዘጋጁ ዕቅዶችን በአግባቡ በመተግበር ተቋማቱ የቆመለትን ግብ ለማሳካት ሰራተኞች መብትና ግዴታቸውን አስመልክቶ ያላቸውን ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመዋል ፡፡ አንዳንድ ሰራተኞች በሰራተኞች መተዳደርያ ደንብ ዙርያ በቂ ግንዛቤ የሌላቸው በመሆኑ በዚህ ሳቢያ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት ታስቦ ስልጠናው መዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡ አቶ ጃምቦ ብርሃኑ ህጉን አስመልክቶ የግንዛቤ ማነስ ናቸው ያሏቸውን በአግባቡ አለመተርጎም ቅሬታ አቀራረብ እንዲሁም አዲስ ተቀጣሪ ሰራተኞች ክሊራንስ እንዲያቀርቡ ሳይደረግ መቅጠር፤ ከሰው ሃብት የስራ ሂደት ዕውቅና ውጪ የስራ ሃላፊዎች ዝም ብሎ ደረጃ ዕድገት መስጠት ዋና ዋና ችግሮች መሆናቸውን ገልፀው ከሰራተኛው የሚጠበቁ ተግባራትንም አብራርተዋል፡፡ ሰልጣኞችም በበኩላቸው በሰው ሃብት አስተዳደር መሰራት ያለባቸውና ሰራተኛው ማወቅ አለበት ያሉትን ተግባራት በስልጠናም ሆነ በተለያየ መንገድ ግንዛቤያቸውን ማሳደግ ይገባል ማለታቸውን የዘገበው የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት የኮሙኒኬሽን ደጋፊ የስራ ሂደት ነው ፡፡