Friday, June 7, 2019

በአዲሱ የግንባታ አሠራር አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑ ተገለፀ፡፡ ዜና ግንቦት 29 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽ/ቤት ለሚገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች አስፈላጊው የግንባታ ግብዓት በሥራ ተቋራጮች እየቀረበ ቤቶቹ የሚገነቡበት አሠራር በመዘርጋቱ አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑ ተገለፀ፡፡ አዲሱ አሠራር በቦሌ አራብሳ ሳይት የግንባታ አፈፃፀሙን ለማፋጠን የጎላ አስተፅኦ ማበርከቱን የልደታ ቅርንጫፍ ፕሮጀክት ጽ/ቤት አመልክቷል፡፡ የቅርንጫፍ ፕሮጀክት ጽ/ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አረጋ አባተ እንደገለፁት ቀደም ሲል የነበረውን ፕሮጀክት ጽ/ቤቱ የግንባታ ግብዓቶችን እያቀረበ የሚያስገነባበትን አካሄድ በመቀየር ግብዓቶቹ በሥራ ተቋራጮች እየቀረበ ግንባታው የሚካሄድበት አሠራር ተግባራዊ በመደረጉ የተሻለ ለውጥ ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ በአዲሱ አሠራር ነው ወደ ሥራ የገባነው ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ በተለይ ለመንግሥት ሠራተኞች በኪራይ ለማስተላለፍ በባሻ ወልዴ እና በገላን ሳይቶች በንፋስ ስልክ ላፍቶ ቅርንጫፍ ፕሮጀክት ጽ/ቤት አማካኝነት በመገንባት ላይ ከሚገኙት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ጠቃሚ ልምድ በመውሰድ ወደ ሥራ መገባቱንም ጠቁመዋል፡፡ የበለስ አማካሪ ድርጅት የፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አሸናፊ ታምራት በበኩላቸው የግንባታ ግብዓቶችን ተቋራጮች እያቀረቡ የሚገነቡበት አዲስ አሠራር መዘርጋቱ ለሥራ ቅልጥፍናም ተመራጭ እንደሆነ አመልክተው ህንፃዎቹን በፍጥነት በማጠናቀቅና ለተጠቃሚዎች ለማድረስ የጎላ አስተዋፅኦ እንዳለው ነው የሚናገሩት፡፡ አዲሱን አሠራር በበለጠ ስኬታማነት ለማከናወን እና ህብረተሰቡን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ መንገድ መብራትና ውሃን የመሰሉ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችንም ትኩረት ሰጥቶ ማሟላት እንደሚገባ የሥራ ኃላፊዎቹ አሳስበዋል፡፡