Sunday, January 13, 2019

የመጀመሪያዉ መንፈቀ አመት ግምገማ

በመጀመሪያው መንፈቀ ዓመት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ ላይ ውይይት ጥር ቀን 2011 ዜና በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽ/ቤት ለ2011 በጀት ዓመት በዕቅድ የተያዙ የግንባታ ተግባራትን ለማሳካት የሚያስችል የተከለሰ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገለፀ፡፡ የፕሮጀክት ጽ/ቤቱ ባለሙያዎችና አመራሮች በመጀመሪያው መንፈቀ ዓመት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡ የፕሮጀክ ጽ/ቤቱ ሠራተኞች ባካሄዱት ውይይት ላይ እንደተገለፀው በ2011 በጀት ዓመት የመጀመሪያው መንፈቀ ዓመት የሥራ ክንውን ላይ የተገኙ መልካም ውጤቶችና ያጋጠሙ ችግሮችን ታሳቢ ያደረገ የተከለሰ ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ ተግባር የተገባ ሲሆን ዕቅዱ በቀጣዮቹ ስድስት ወራት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የፕሮጀክት ጽ/ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ኪሮስ መሰለ እንዳመለከቱት በተለያዩ ሳይቶች ግንባታቸው እየተፋጠነ ያሉት የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ተመዝግበው በመጠባበቅ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ለማድረስ እየተደረገ ያለው ርብርብ የሚበረታታና ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ነው፡፡ የፕሮጀክት ጽ/ቤቱ የጥናት፣ ዕቅድና በጀት የሥራ ሂደት መሪ አቶ ተዘከር ፀጋዬ በውይይቱ ላይ ባቀረቡት የስድስት ወራት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት በተለይ ግንባታቸው ባለፈው የ2010 በጀት ዓመት የተጀመሩት ከአንድ ሺህ ሰባት መቶ በላይ ለኪራይ የሚቀርቡ ቤቶች በአሁኑ ወቅት ከ91 በመቶ በላይ መድረሳቸው መልካም ተሞክሮ በመሆኑ ወደ ሌሎች ግንባታዎችም ሊስፋፋ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ ሪፖርቱን ተከትሎ የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰነዘሯቸው አስተያየቶችና ጥያቄዎች መንገድ፣ መብራትና ውሃን የመሰሉ የመሠረተ ልማት አቅርቦቶች አለመሟላት እንዲሁም የግንባታ ግብዓት አቅርቦት እጥረትና ሌሎችም ተያያዥ ችግሮች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ የጠቆሙ ሲሆን ከመድረኩ ምላሽ ተሰጥቶባቿል፡፡ በፕሮጀክት ጽ/ቤቱ ያለው መልካም አስተዳደር በሚፈለገው ደረጃ እንዲሆን የህብረተሰቡን እርካታ መሠረት ያደረገ ፈጣን ምላሽ በመስጠት የተገልጋዮችን እርካታ ለማረጋገጥ ይበልጥ ጠንክሮ መሥራት እንደሚያስፈልግና በየደረጃው የሚገኙ ባለሙያዎችና ኃላፊዎችም ሥራቸውን በባለቤትነት ስሜት ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው ተጠቁሟል፡፡ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽ/ቤት በተለያዩ ሳይቶች ከ94 ሺህ በላይ ቤቶች በመገንባት ላይ እንደሚገኝ የፕሮጀክት ጽ/ቤቱ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ደጋፊ የሥራ ሂደት ዘግቧል፡፡

No comments:

Post a Comment